ምስጢረ ከዋክብት
ከብዙ ሽህ ዓመታት በፊት የሥነ ፈለክ ሶይንስ ሲጀመር የጨረቃን፣ የፀሐይን የፕላኔቶችንና የከዋክብትን አጓጓዝ ለመከታተል እና ለማስረዳት ነው። በአሁኑ ግዜ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ትልቁ ሥራቸው ለምን ይህ ወይም ያ የሥነፈለክ ክስተት ሆነ ወይም አልሆነም ? ከዋክብት እንዴት የብርሃን ምንጭ መሆን ቻሉ ? ከዋክብት ከየት መጡ ከምንስ ተስሩ ? እያሉ መጠየቅና መልሶቻቸውን ማስላት ነው። እንግዲህ በጥቅሉ የሥነ ፈለክ ዋናው ስራ የከዋክብት ሕግጋትን ማወቅና የጠፈርን ሚስጥር ፈልፍሎ ማውጣት ነው ተብሎ ቢታሰብ መልካም ነው ። በዚህ ዓይነት ሲታይ የሥነፈለክ ተመራማሪ ለመሆን ጥብቅ ተግባራዊ የሆነ የፊዚክስ የሒሳብ የኬሚስትሪና የባዮሎጂ ትምህርት አስፈላጊ ናቸው።
ይህ በዚህ እንዳለ የሰው ልጅ የሳይንስ እውቀት ኖረውም አልኖረውም ስለ ህልውናው ብዙ ጥያቄዎች ይጠይቃል ከየት መጣሁ? ወዴት እየሄድኩ ነው? ተፈጥሮ ምንድነው? ከየት መጣ? ማን ፈጠረው ? ለሚሉት ጥያቄዎቹ በሚገነዘበው የተፈጥሮ ቅጥ (ፓተርን) እምነቱንና የሚከተለውን ህብረተሰባዊ ስርዓት ተከትሎ መልስ ይሰጣል ።ለምሳሌ የወቅቶች መቀያየር የጨረቃ መልክ መለዋወጥ የጸሃይ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃን መለያየት የመሳሰሉት በተመልካች ላይ ከባድ የምርምር ጥያቄዎች ያስነሳሉ። በዚህ አምድ አንድ ሰው ሊጠይቀው የሚችለውን አንድ ጥያቄ አንስተን በጥንት አባቶቻቸን የተሰጠውን መልስ እናያለን።
ጥያቄ፡ ጸሃይ ታበራለች ትሞቃለች ጨረቃና ከዋክብትም ያበራሉ ግን ብርሃናቸው ቀዝቃዛ ነው ይህ የሆነበት ምክንያቱ ምንድነው ? ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ስማይን እንቃኝ።
ሰማይን እንቃኝ፡ ከዋክብትና ሕብረ ከዋክብት
ከዋክብት እንዳቀማመጣቸው በሕብረ ከዋክብት ውስጥ ተመድበዋል። ፰፰ የታወቁ ሕብረ ከዋክብት አሉ። ከነዚህ ውስጥ ፬፰ቱ ጥንታዊነት አላቸው። አንድ ሕብረ ከዋክብት ዉስጡ ላለ አንድ ኮከብ አድራሻ ነው። ለምሳሌ ኩሽቶፒያ ወይም ካኢሶፒያ ወይም ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀው ሕብረ ከዋክብት ውስጥ ካሉት ከዋክብት እጅግ ደማቁ ኮከብ a-ኢትዮጵያ (a-Cassiopea) ተብሎ ይጠራል።
እንደ ወግ እና ባህል የሕብረ ከዋክብቶች ጥቅምና ወስጣቸው ያሉት ከዋክብት አጠራር ይለያያል። ወቅቱ በተቀያየረ ቁጥር የሕብረ ከዋክብቱ አቀማመጥ ይቀያየራል ለምሳሌ ምስሉ እንድሚያሳየው የኢትዮጵያ ሕብረ ከዋክብት ወቅቱ በተቀየረ ቁጥር ቅረጹ አንዳንዴ ሠ ን አንዳንዴ ደግሞ ጠ ን ለመምሰል ይቃጣዋል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ይህቺን ቅርጽ ይዞ ቢቆይም ዘመናዊው ሥነፈለክ በቢጫ የተከበውን ወስን ሰጥቶታል።
ፐርሲየስ፤ አንድሮሜዳ (ብሩክታይት) እና ሲፍዩስ (የኢትዮጵያ ንጉስ) ያዋስኑታል። የጥንት የሰማይ ባላባቶች የግሪክ የግብጽ የባቢሎን የሲኖ የኑቢ የዓረብ ሰዎች ናቸው ይባላል። ነገር ግን በብዛት ያልታወቁ ራሳቸውን የቻሉ ከማንም የማያንስ ከዋክብትን እና ሕብረ ከዋክብትን አቀማመጣቸውን እና አጓጓዛቸውን እያጠኑ ከብዙ ሺህ አመታት ጀምሮ ተፈጥሮን አሸንፈው እስከ አሁን ያሉ ነባር ጎሳዎች እንዳሉ ዘመናዊ ታሪክ ያስረዳል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሥነ ፈላክ የተፈጥሮ እውቅት ካላቸው መካከል ኮንሶ፤ሙርሲ፤ቦረና፤በኤርትራ ደግሞ ትግረ የመሳሰሉት ጎሳዎች በባህላዊ ሥነፈለክ ጥናት ውስጥ በብዛት ይጠቀሳሉ።
ወደፊት ይህንን ጉዳይ በሰፊው እናጠናዋለን። ከ፬፰ ቱ ፩፪ቱ ዞዲያክ ሕብረ ከዋክብት ወይም በሄኖክ አባባል ፩፪ቱ ደጃፎች የሚባሉት ናቸው። ከዚህ በታች የሚታየው ምስል የ12ቱን ደጃፎች አቀማመጥና የጸሃይን (ብጫ) ፈር እና የመሬትን (ሰማያዊ) ፈር ያሳያል።
ወቅቶች ሲቀያየሩ በምሽት የምናያቸው ሕብረ ከዋክብትም ይቀያየራሉ። በኢትዮጵያ ከመስከረም ጀምሮ እስከመጋቢት ወር ድረስ ሑት ሐመል ሰውር ገውዝ ሽርጣንና አሰድ ይታያሉ። እነዚህ የምዕራብ ደጃፎች ሲሆኑ የምስራቅ ደጃፎች የቀሩት ይሆናሉ እንግዲህ ጸሃይ በምዕራብ በኩል ስድስት ወር በምስራቅ በኩል ስድስት ወር ትቆያለች ማለት ነው- አንዱን ህብረ ከዋክብት ለማለፍ አንድ ወር ያክል ይፈጅባታል። አሁን ደግም 12ቱን ደጃፎች በሶስት ሲከፍሉት አራት አራት ይደርሳል ይህም አራቱን ወቅቶች ያመጣል:- እንሱም መጸው ጸደይ ሓጋይ (በጋ) ና ክረምት ናቸው። በዓውደ ነገስት አቡሻከርና በመጽሃፈ ሄኖክ በሚባሉት መጻሕፍት ውስጥ የ12ቱ ዞዲያክ የሕብረ ከዋክብት ዝርዝር ተጽፏል።
የከዋክብት ድምቀት ዋጋ ፡ የዕውን ድምቀት (Apparent Magnitude)
የስው ዐይን ያለአጉሊ መነጽር 6000 የሚሆኑ ክዋክብትን ማየት ይችላል። ከዚህ በታች ያለው ምስል የሚያሳየው የሰማይን 5% (፸ዲX፵፮ዲ) ያክል ነው።
ጥቋቁሮቹ ነጠብጣቦች ያለ አጉሊ መነጽር ሊታዩ የሚችሉ ከዋክብት ናቸው። በዘመናዊ አስራር የኮከብ ድምቀት ስድስት ደረጃ አለው ፩ኛ ደረጃ በጣም ድምቅ ያለ ሲሆን ፮ኛ ደረጃ የሆነው ደግሞ በጣም የደበዘዘ ሆኖ ጤነኛ ዓይን ከ፮ኛ ድረጃ በታች ማየት አይችልም።ሁለት ከዋክብት የደረጃ ልዩነታቸው ለምሳሌ ፩ ቢሆን አንዱ ኮኮበ ከሌላው ፻ ጊዜ ይደምቃል ወይም ይደበዝዛል ማለት ነው ። ይህቺን ኖት ለማጠቃለል በጥንት ግዜ ኢትዮጵያውያን የከዋክብትን ድምቀት መለያየት እንዴት አሰሉት የሚለውን ጥያቄ እንመልስላለን። ይሄንን ጉዳይ ከመጻህፈ ሄኖክ ማግኝት ይቻላል ። ነገሩ እንደዚህ ነው ሄኖክ በኡራኤል አማክይነት ወደሰማይ ሄዶ ብዙ ነገሮችን ተምሯል ተገንዝቧል። እነዚህም ከዋክብት ጸሃይም ሆነ ጨረቃ አጓጓዛቸውን ሃይላቸውን ግንኙነታቸውን ወቅታዊ አወጣጣቸውን ህጋቸውን ስማቸውን ተገንዝቧል። በተጨማሪም የጸሃይን ጉዞ ከምስራቅ ወጥታ በምዕራብ እንደምትገባ በየወቅቱ የምታልፍባቸው ደጃፎችና ስማቸውን አውቋል። በተጨማሪም በነዚህ ደጃፎ ጨረቃም እንደምትጓዝ አውቋል። በተጨማሪም ጸሃይ ከሚነድ ነፋስ መሰራቷንና፤ የጸሃይ የከዋክብትና የጨረቃ ሃይል ልዩነትን በሒሳብ ተምሯል። ይህን ሒሳብ የኢትዮጵያን የከዋክብት ዕውን ድምቀት መለኪያ አድርጎ ማሰብ ይቻላል።
የቅዱስ ሄኖክ የከዋክብት የጨረቃና የጸሃይ ዕውን ድምቀት ስሌት
የጸሃይ ተፈጥሮ ከእሳትና ከነፋስ ነው ። ጨረቃንና ከዋክብትን ከነፋስና ከውሃ አደረጋቸው እንዲህ አድርጎ ለይኩን ብሎ ከፈጠረው ከደገኛው ብርሃን ፈጠራቸው። የሃይላቸውን መጠን እንደሚከተለው አደላደላቸው ፤-የአንዲት የስንዴ ቅንጣት ያክል አምጥቶ ከሰባት ከፈለና ስድስቱን እጅ ለጸሓይ አደረገ። የቀረውን አንድ እጅ ከሰባት ከፍሎ ስድስቱን እጅ ለጨረቃ አንዱን እጅ ለከዋክብት አደረገ። በዚህ ምክንያት ሃይላቸው ወይም ድምቀታቸው ሊለያይ ቻለ።
በሒሳብ—– የጸሃይ ሃይል =6/7 የጨረቃ ሃይል =6/49 የከዋክብት ሃይል=1/49
በዚህ ስሌት ጸሃይ ጨረቃን ፯ ጊዜ በድምቀት ትበልጣታለች። ሁሉም ከዋክብት አንድ ጋር ሆነው ደግሞ ጸሃይ ፵፪ ጊዜ በድምቀት ትበልጣቸዋለች ማለት ነው።አሁን ለመዝናኛ ያክል በግጥም ሚስጥረ ከዋክብትን እንናገራለን።
ምስጢረ ከዋክብት–አበበ ከበደ
ሰማይና መሬት የትገናኙበት
ምንድን ይሆን ህጉ ሚስጥረ ከዋክብት
ጸሃይ ሰትጨልም ጠብቃ ሰአት
ቀን ቀንን ጨርሶ ሲመጣ ምሽት
የቤተክሲያን ደወል ሲያበስር ጸሎት
ሃሌ ሃሌ ሉያ ሃይማኖተ አባት
ጸጥ እርጭ ሆኖ ሁልም በያለበት
ድፍን ባለ ሌሊት በከዋክብት ብርሃን
የቆሎ ተማሪ ከፍ አድርጎ ድምጹን
በገበዙ ትዛዝ ሲዘርፍ ቅኔውን
ምንድ ነው ሚስጥሩ ሃሳበ ከዋክብት
የትጋ ነው ወሰኑ ሰማየ ሰማያት
ሄኖክ አባታችን እንድሚያሰተምረን
እያንዳዱ ኮከብ አለው ትልቅ መጠን
ምንም ቢደበዝዝ ትንሽ ቢመስል
ከጸሃይ የሚበልጥ ያመንጫል ሃይል
አጥሩን አጠረ በ ህብረ ከዋክብት
ሰማየ ሰማያት መግቢያው አስራ ሁለት
ስድስቱን በምስራቅ በምራብ ስድስት
ከረምትና በጋ ቁርና ሀሩር
ተብለው ተከፍለው በሶስት ሶስት በር
ሁሉም በየወቅቱ ይወጣል ይገባል
የአምላክን ትዛዝ ስራት በመከተል
የጨረቃ ደምቀት የጸሃይ ሙቀት
የከዋክብት ማነስ የሃይል ልዩነት
ምን ይሆን ትዛዙ ስነስርእት
አንድ ፍሬ ስንዴ ክፈለው ሰባት
ስዱስትን ለጸሃይ እንዷን ለቀሩት
አንድ ቅንጣት ወስደህ ከፈለው ሰባት
ሰድስቱን ለቀመር አንድ ለከዋክብት
ይኽው ነው ስራቱ ሰማየ ሰማያት
እያለ አስተማረው ሊቀ ልቃውንት
የቆሎ ተማሪ ቀሰመ እውቀት
በጨረቃ ብርሃን ጭር ባለ ሌሊት
ማስተባበያ (DISCLAIMER)
ይህንን ለመጻፍ ለገፋፉኝ የቅንዲል ወዳጆቼ ምስጋና አቀርባለሁ። ይህ ጉዳይ ትልቅ ምርምርንና ትምህርትን የሚጠይቅ በመሆኑ ይህንን ሳቀርብ አልፎ አልፎ ስህተቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ አንባቢዎች እርማታችሁን እንደምትለግሱኝ ሙሉ ተስፋ አለኝ።
ዋቢ (REFERENE)
ስለ ሥነፈለክ በተለይ ስለኢትዮጵያ ጉዳይ በበዛት የተጻፉ መጽሃፍትና ሰነዶች አሉ ። እንዚህን በቀላሉ በጉግል ማግኘ ይቻላል። ይህ ጅምር ስለሆነ ማናቸውንም ጥያቄና ሃሳብ ልውውጥ በፌስቡክ ግሩፕ ላይ ማንሳት ይቻላል።
ጸሃፊውን ለማግኘት
Email: Abekebede@gmail.com
Facebook group: https://www.facebook.com/groups/assan1/
Astronomers by Tradition